ኔፕ ፕላስ ኤች አይቪ /ኤድስን ለመከላከል   የሚያደርገውን ትግል አጠናክሮ ለመቀጠል ዳግም  አረጋገጠ

( ህዳር 22 ቀን 2017፣ ኔፕ ፒአር   እና ኮሚኒኬሽን ፣ አዲስ አበባ

አሁንም ቫይረሱን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የምናደርገውን ርብርብ በመላ አገሪቱ አጠናክረን እንቀጥላለን ስሉ አቶ ካሳሁነ ታደሰ ዳግም  አረጋገጡ፡፡ አቶ ካሳሁን ታደሰ የኔፕ ፕላስ ኤክስክዩቲቭ ዳይሬክተር  ይህንን ያረጋገጡት በአገራችን ለ36ኛ ጊዜ በአለም አቀፍ ደረጃ ደግመ ለ37ኛ ጊዜ በዚሁ በአዲስ አበባ ከተማ በአደዋ ዜሮ ዜሮ አዳራሽ በርካታ የመንግስት በለስልጣናት፤ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተወካዮች እና ጥሪ የተደረገላቸው የህብረተሰብ አካላት በተገኙበት በደማቅ ሥነ ሥርአት  ታስቦ በዋለው የአለም አቀፉ ኤድስ ቀን ላይ ቫይረሱ በደማቸው ያለባቸውን ወገኖች በመወከል  ባስተላለፉት መልዕክት ነው፡፡ በዚህ ሰብአዎ መብትን ያከበረ የኤች አይ ቪ አገልግሎት ለሁሉም በሚል መሪ ቃል በተሰናደው በአል  ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት አቶ ካሳሁን ታደሰ ሥራችን አጠናክረን ለመቀጠል  በድጋሚ ቃል ስንገባ የመንግስትም ሆነ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ድጋፍ እንደ ወትሮው ሁሉ እንደማይለየን በመተማመን ነው ብለዋል፡፡

አቶ ካሳሁን በዚሁ መልዕክታቸው  በየአስተዳደር እርከኑ ከፌዴራል እስከ ታችኛው ቀበሌ አስተዳደር  የሚትንቀሳቀሱ የመንግስትም ሆነ መንግስታዊ ያልሆናችሁ ድርጅቶች፤ ሲቪክ ማህበራት ከማህበሮቻችን ጎን በመቆም፤ ያሉባቸውን የሀብትም ሆነ የአቅም ችገሮችን በመፍታት በአርአያነት በዚህ ቫይረስ ላይ ክንዳቸውን እንዲያበረቱ እንድታግዙአቸው ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ቫይረሱን ለመከላከልና ጉዳቶቹን ለመቆጣጠር  የምናደረገው ጥረትም የተቀዛቀዘ ነው ያሉት ዳይሬከቱ በሽታው  አገርሽቶ አገራችንን ዳግም ዋጋ  እንዳያስከፍለን በተቀናጀና በተደረጀ አመራር እንድሁም ግልፅና ተጠያቂነት ያለበትን አሰራር በመዘርጋት ኃላፊነታችንን እንድንወጣ በማክበር እንጠይቃለሁ  ሲሉ  አሳስበዋል ፡፡ ስለዚህ ሁሉም የሚመለከተው አካላት ሁሉ ትኩረት እንዲሰጡትና፤ በየደረጃው የሚገኙ የኤች አይ ቪ ም/ቤቶች መልሰው እንዲጠናከሩ በአንክሮ እጠይቃለሁ በማለት ንግግራቸውን ደምድመዋል፡፡፡፡

ኔፕ ፕላስ ላለፉት 20 ዓመታት ኤችአይ ቪ/ኤድስን በመከላከልና በመቆጣጠር ሥራ ላይ በሰፊው ሲሳተፍ የቆዬና በርካታ ውጤቶችን ያስገኘ አንጋፋ  ድርጅት ነው፡፡