ዶ/ር ብሩክ አለማየሁ (የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት)
በአለማችን ከ38ሚሊየን የሚበልጥ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ኤች.አይ.ቪ.(HIV) በደማቸው ውስጥ ይኖራሉ፡፡ ከዚህ ውስጥ ሁለት ሶስተኛው የሚገኙት በአህጉራችን አፍሪካ ሲሆን የሀገራችንም ሁኔታ ብዙም ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ በኢትየጵያ ከ4 ወራት በፊት እንደተገለፀው በቫይረሱ እየተያዙ ያሉ አዳዲስ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንደሚገኝና ከሶስት ክልሎች ውጪ በቀሩት የአገሪቱ ክፍሎች በወረርሽኝ ደረጃ ይገኛል፡፡
ከሰሞነኛው የኮቪድ19 ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ የኤች.አይ.ቪ ታካሚዎቻችን የሚያነሷቸውን
ጥያቄዎች ለመመለስ
ሞክረናል፡፡
ጥያቄዎቻቸውና መልሶቹ እንደሚከተለው ቀርበዋል
ጥያቄ 1 ፡- ኤች.አይ.ቪ. (HIV) በደሜ ውስጥ እንዳለ ተነግሮኛል:: ነገር ግን መድሃኒት አልጀመርኩም፡፡ ምን ላድርግ?
መልስ፡– ከዚህ በፊትም ይሁን በአሁኑ ወቅት HIV በደማቸው እንዳለባቸው ተነገሯቸው የህክምና ክትትል ወይም መድሃኒት ያልጀመሩ ታካሚዎች በቶሎ ሀኪም አንዲያማክሩና እና ልዩ ምክንያት ወይም ሕክምና እንዳይጀምሩ የሚከለክል የጤና ችግር ከሌለ በስተቀር የፀረ ኤች.አይ.ቪ. (HIV) መድሃኒቶችን እንዲጀምሩ ይመከራል፡፡
ከኮቪድ አንፃር ልዩ መረጃ ባይኖርም አነዚህን መድኃኒቶች መጀመር የሰውነት የመከላከል አቅም እንዲጎለብትና ሰውነታችን ለተለያዩ ተጓዳኝ ኢንፌክሽኖች እንዳይጋለጥ ይረዳል፡፡ የፀረ ኤች.አይ.ቪ. መድሃኒት የሲደ4 (CD4) ቁጥር አነሰም በዛም በየትኛውም ደረጃ መጀመር አለበት፡፡
ጥያቄ 2. በኤች.አይ.ቪ. (HIV) የተያዙ ሰዎች በኮቪድ19 የመያዝ እድላቸው ከሌላው አንፃር የበለጠ ነው?
ባጠቃላይ መድሃኒት ያልጀመሩ፣ ሲዲ4(CD4) ቁጥራቸው ዝቅተኛ የሆነ እና በደማቸው ያለው የቫይረስ መጠን (Viral Load) ከፍተኛ የሆኑ የኤች.አይ.ቪ. ታካሚዎች ለሌሎች ኢንፌክሽኖች የበለጠ ተጋላጭ እንደሆኑ ይታወቃል፡፡ በተጨማሪም እድሜያቸው የገፋና ተደራራቢ ህመም ያለባቸው ሰዎች በኮቪድ19 ከተያዙ ጠንከር ባለ ሁኔታ ሊታመሙ የሚችሉበት እድል ሰፊ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን እስካሁን ድረስ ኤች.አይ.ቪ. እና ኮቪድ19 መሀከል ያለውን መስተጋብር ያሳየ ልዩ መረጃ የለም፡፡
በተለይም መድሃኒት እየወሰዱ ያሉና ጥሩ ቁጥጥር ላይ ያሉ ታካሚዎች ከጤነኛ ሰው የተለየ ተጋላጭነት አላቸው ተብሎ አይታሰብም፡፡ ይሁንና ያለው መረጃ በቂ ካለመሆኑ አንፃር እና ከዚህ በፊት የተከሰቱ መሰል ወረርሽኞች ካደረሱት አደጋ አንፃር ታማሚዎች በቂ ጥንቃቄዎችን ማድረግ አለባቸው፡፡
የመረጃ ውስንነቱ እንዳለ ሆኖ በተለይ ሲዲ4(CD4) ቁጥራቸው ዝቅተኛ የሆነ እና በደማቸው ያለው የቫይረስ መጠን (Viral Load) ከፍተኛ የሆኑ ታካሚዎች ለጠና ህመም የተጋለጡ ናቸው ተብሎ ይታሰባል፡፡
ከኤች.አይ.ቪ በተጨማሪም የታካሚው እድሜና ሌሎች ቋሚ ህመሞችም ተጨማሪ ሚና እንደሚኖራቸው መረሳት የለበትም፡፡
ጥያቄ 3. የ ኤች.አይ.ቪ. (HIV) ታካሚዎች ራሳቸውን ከኮቪድ 19 ለመከላከል ምን ማድረግ አለባቸው?
ባሁኑ ሰዓት ኮቪድ19 ክትባት የለውም፡፡ ብቸኛው የመከላከያ መንገድ በቫይረሱ ላለመያዝ እራስን መጠበቅ ነው፡፡ ይህንንም ለማድረግ መደበኞቹን የመከላከያ መንገዶች በአግባቡ መተግበር ለሁሉም የኤች.አይ.ቪ. (HIV) ታካሚዎች ይመከራል፡፡ እነዚህም፡-
- ሳል፣ ትኩሳት እና ጉንፋን መሰል ህመም ካላቸው ሰዎች መራቅ
- በአግባቡና በተደጋጋሚ እጅን መታጠብ/በአልኮል ማፅዳት
- ባልታጠበ እጅ አፍ፣ አፍንጫ ወይም ዓይንን አለመንካት
- ሰዎች በሚሰበሰቡባቸው ቦታዎች አለመገኘት
- አላስፈላጊ ጉዞዎችንና እንቅስቃሴዎችን ማስቀረት
- ከዚህም በተጨማሪ
- የተመጣጠነ ምግብ መመገብ
- በቂ እንቅልፍ/እረፍት ማግኘት
- በተቻለ መጠን ውጥረትን መቀነስ
- መድኃኒት ሳይረሱና ሰዓት ሳያሳስቱ በየዕለቱ መዋጥ
- ለወራት የሚያቆይ በቂ መድኃኒት እጅ ላይ መያዝ
- ልዩ ስሜት/ችግር ካለ ከሀኪም ጋር መመካከር
ጥያቄ 4. የ ኤች.አይ.ቪ. (HIV) ታካሚ ነኝ፡፡ ሁልጊዜ ማስክ ማድረግ አለብኝ ወይ?
ማስክ ማን ያድርግ ማን አያድርግ የሚለው ነገር ብዙ ግርታ ያለው ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ እየወጡ ያሉ መረጃዎችን ተከትሎ ማንኛውም ሰው ከቤት ሲወጣ በተለይም ደግሞ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ በማይችልበት ሁኔታ ላይ ማስክ ቢያደርግ መልካም ነው፡፡ ይህ ምክረ ሀሳብ በሁሉም የኤች.አይ.ቪ. ታካሚዎችም ቢተገበር የተሻለ ነው፡፡
ጥያቄ 5. የ ኤች.አይ.ቪ. (HIV) ታካሚ ነኝ፡፡ በኮቪድ19 እንደተያዝኩ እጠረጥራለሁ፡፡ ምን ማድረግ አለብኝ?
አንድ ሰው የኮቪድ 19 ምልክቶች ከታዩበት በተቻለ መጠን በቶሎ ከሀኪሙ ጋር (በስልክና በአመቺ መንገድ) ሊመካከር ይገባዋል፡፡ ከዚያ በተጨማሪ ግን የኮቪድ19 ምልክቶች ከታዩበት ሊያደርጋቸው የሚገቡ ጥንቃቆዎችና ሂደቶች በሚገባ ተግባራዊ ማድረግ ይጠቅማል፡፡
ጥያቄ 6. የፀረ ኤች.አይ.ቪ. (HIV) መድሃኒቶች ኮቪድ19ን ለማከም ይጠቅማሉ?
አንዳንድ የፀረ ኤች.አይ.ቪ. (HIV) መድሃኒቶች ኮቪድን ለማከም ጥናት እየተደረገባቸው እንደሆነ ተነስቷል፡፡
ከዚህ አንፃር በተለይ የሚነሳው ካሌትራ [Kaletra(Lopinavir boosted with Ritonavir (LPV/r))] ነው፡፡ መጀመሪያ ላይ አበረታች ውጤት እያስገኘ ነው ተብሎለት የነበረ ቢሆንም ከቻይና በወጡ አንዳንድ ጥናቶች መሰረት ግን የተጠበቀውን ያህል ውጤት አላሳየም፡፡ ይሄ እና ሌሎች የኤች.አይ.ቪ መድሃኒቶች ላይ ከ15 በላይ ጥናቶች እየተካሄዱ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ውጤቶቹን መጠበቅ መልካም ነው፡፡
ጥያቄ7. በኮቪድ19 እንዳልያዝ የሚከላከልልኝ የፀረ ኤች.አይ.ቪ. (HIV) መድሃኒት አለ? የምወስደው መድሃኒት ሌላ ከሆነስ መድሃኒቴን ማስቀየር ይጠቅመኛል?
ኮቪድ19ን ይከላከላል በሚል መድሃኒታቸውን ወደ ካሌትራ ለማስቀየር ጥያቄ የሚያቀርቡ ታካሚዎች ብዙም ባይሆኑም አሉ፡፡ ይህንን በተመለከተም ያለው ጥናት አጅግ ደካማ ነው፡፡
በተለይ ካሌትራ ካሉት የጎንዮሽ ችግሮች አንፃር ኮቪድ19ን ለመከላከል ከሚል ሃሳብ ብቻ ተነስቶ መድሃኒትን ወደ እሱ ማስቀየር በፍፁም አይመከርም፡፡
ጥያቄ8. ሀገራት የፀረ ኤች.አይ.ቪ. (HIV) መድሃኒቶችን ኮቪድ19ን ለማከም ከተጠቀሙ እጥረት ሊከሰት አይችልም ወይ?
አሁን ባለንበት ሁኔታ ይህ ትልቅ ስጋት ነው ተብሎ አይታሰብም፡፡ ምክንያቱም ካሌትራን በስፋት ለኮቪድ19 እየተጠቀምንበት ስላልሆነ እና ካሌትራን የሚጠቀሙ የኤች.አይ.ቪ. ታካሚዎች ጥቂት በመሆናቸው ነው፡፡
ይሁንና ብዙ የኮቪድ19 ታካሚዎችን በእዚህ እና ሌሎች ፀረ ኤች.አይ.ቪ. መድሃኒቶች ማከም የምንጀምር ከሆነ የመድሃኒት እጥረት ሊከሰት የሚችልበት እድል አለ፡፡ ስለዚህም ሀገራት ይህንን ጉዳይ በቅርበት ሊከታተሉ እና እጥረት እንዳይከሰት የተለያዩ አማራጮችን መጠቀም ይኖርባቸዋል፡፡
የጤና ወግ