ኔትዎርክ ኦፍ ኔትዎርክስ ኦፍ ኤች አይ ቪ ፖዘቲቭስ ኢን አትዮጵያ (ኔፕፕላስ) አዲስ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ሾመ፡፡ የኔፕፕላስ ስራ አመራር ቦርድ የካቲት 1 አና 2 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ኢንተር ሌግዠሪ ሆቴል ባካሄደው ስብሰባ ከቀረቡት አጩዎች መካከል አቶ ካሳሁን ታደሰን ባላቸው የስራ ልምድ፤ ክህሎት እና ብቃት ለቦታው ብቁ መሆናቸውን በማረጋገጡ የድርጅቱ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር አድርጎ ሾሟል፡፡ የኔፕፕላስ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ አብዱረሃማን ከማል እንደገለጹትም ለቦታው ከቀረቡት እጩዎች መካከል አቶ ካሳሁን ድርጅቱን ወደ ላቀ ደረጃ ከፍ እንደሚያደርጉት በመተማመን የስራ አመራር ቦርዱ በሙሉ ድምጽ የድርጅቱ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር አድርጎ ሾሟቸዋል፡፡
አቶ ካሳሁን ታደሰ አዲሱ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር
አቶ ካሳሁን ታደሰ የትምህርት ዝግጅታቸውን ስንመለከት የመጀመሪያ ድግሪያቸውን በማኔጅመንት ያገኙ ሲሆን፤ በቢዝነስ ደግሞ የማስተርስ ድግሪያቸውን ሰርተዋል፡፡ በተጨማሪም በፐብሊክ ኸልዝ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ እና ጥናቶችን በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡ አቶ ካሳሁን በስራው አለም በአጠቃላይ ወደ 17 አመታት ልምድ ያላቸው ሲሆን፤ ከእንዚህ ውስጥም ዋና ዋናዎቹ የኢትዮ ላይፍ ሴቪንግ አሶሲየሽን መስራች እና ጀነራል ማናጀር ሲሆኑ በተለያዩ ትላልቅ ድርጅቶች ውስጥም በተለያየ የሃላፊነት ቦታዎች አገልግለዋል፡፡ ከእንዚህ ተቋማት መካክልም በኔትዎርክ ኦፍ ኔትዎርክስ ኦፍ ኤች አይ ቪ ፖዘቲቭስ ኢን ኢትዮጵያ በኤክስኮዩቲቭ ዳይርክተርነት እንዲሁም በህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ማናጀርነት ፤ በኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ አይ ካፕ ኢን ኢትዮጵያ በአድሄረንስ ሰፖርተርነት አማካሪ እና አድሄረንስ ኬዝ ማናጀመንት ፕሮግራም ኤክስፐርት ናቸው፡፡
ለዚህ ሃላፊነት መመጣቸውን ተከትሎ ድርጅቱን አሁን ካለበት ወደ ላቀ ደረጃ ከፍ ለማድረግ የአጭር ጊዜ እቅዶችን መያዛቸውን የገለጹልን አቶ ካሳሁን ፤ ይሄንን ለማሳካተም የድርጅቱን የውስጥ አቅም ማደራጀት፤ የኔትዎርኩንና የክልል ኔትዎረኮችን አቅም በቴክኒክ፤ በእውቀት እንዲሁም በክህሎት ማጠናከር፤ ከለጋሾችና ከአጋር ደርጅቶች ጋር የነበረውንና የተቋረጠውን ግንኙነት መልሶ በማስቀጠል ሃብት የማበልጸግ ስራዎችን ለመስራት ማቀዳቸውን ገልጸውልናል፡፡ ኔፕፕላስ ምንም እንኳን እውቅና የተሰጠው ትልቅ ድርጅት ቢሆንም በመንግስት በኩል እስካሁን ድረስ ፋይል ያልተከፈተለት በመሆኑ በቀጣይ ግን ፋይል ተከፍቶለት ጤና ሚኒስቴር በየአመቱ ከሚመደብለት በጀት ላይ አመታዊ በጀት እንዲመድብለት ለማድረግ በርካታ ስራዎችን የመስራት እቅድ እንዳላቸው እንዲሁም የደርጅቱን መተዳደሪያ ደንብ፤ ፖሊሲ እና ስትራቴጂክ ፕላን ዘመኑን በዋጀ ምልኩ የመከለስ እና የማዘጋጀት ስራዎች ይሰራሉ ብለዋል አቶ ካሳሁን፡፡
ምንም እንኳን እነዚህንና ሌሎች ተግባራትን ለማከናወን በከፍተኛ ዝግጅት የመጡ ቢሆንም የተወሰኑ ተግዳሮቶች ሊገጥሟቸው እንደሚችሉ የገለጹት አቶ ካሳሁን፤ እነዚህን ችግሮች በተገቢው መንገድ ለመቋቋም መዘጋጀታቸውንም አስረድተዋል፡፡ የመጀመሪያው ሊገጥም የሚችለው ተግዳሮት የታሰበውን እና አስፈላጊውን ያህል ሃብት የማግኘት ችግር ሲሆን፤ ይሔ ችግርም በተለያየመልኩ ይፈታል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም በድርጅቱ ውስጥም ሆነ በክልል ኔትዎርኮች ውስጥ ያለውን የጥቅም ግጭት ለመፍታት በቴክኒክ፤ በእውቀት እና በክህሎት የአቅም ማጎልበት ስራዎች ይሰራሉ እንደ አቶ ካሳሁን ገለጻ፡፡ ሌላው ሊገጥም ይችላል ያሉት ተግዳሮት ለጋሾች በየጊዜው መቀያየራቸው የየራሳቸውን ባሕሪ ይዘው ስለሚመጡ ያንን ጫና ለመቋቋምና ተመቅረፍ የሃገር ውስጥ ሃብት የማፈላለግ ስራም ትኩረት ተሰጥቶት እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡ ክልሎች የተመደበላቸውን ሃብት በእግባቡ አለመጠቀም ሌላው ሊገጥም የሚችል ተግዳሮት መሆኑን የገለጹት አቶ ካሳሁን ይሄንንም በተለያየ መንገድ ለመቅረፍ መዘጋጀታቸውን አብራርተዋል፡፡
በመጨረሻም ኔፕፕላስ በሃገር አቀፍ ደረጃ ቫይረሱ ያለባቸውን በርካታ ወገኖች ያቀፈ ዣንጥላ አንደመሆኑ የግል ጥቅምን ሳይሆን የማህበረሰቡን ድምጽ ለማሰማት እና ቫይረሱ ያለባቸው ወገኖች የተሻለ ህክምና በማግኘት የተሻለ ህይወት እንዲኖሩ የሚረዳ፤ በመንግሽጽና በኅዝብ መካከል ድልድይ በመሆን የመንግስትንም ጫና የሚቀንስ ሃገር አቀፍ ድርጅት እንደመሆኑ; ሁሉም አካል በእኔነትና ይመለከተኛል በሚል ስሜት እጅና ጓንት ሆኖ በትብብር ሊሰራ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ ሁሉም በኔትዎርኩ ዙሪያ ያለ አካል አንድ በመሆን የግል ስሜትን ሳይሆን የማህበረሰቡን ጥቅም በማስቀደም እና በአገልጋይነት ስሜት ሃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባም መክረዋል፡፡