በኢትዮጵያ የዩኤን ኤድስ ካንትሪ ዳይሬክተር እና ተወካይ ዶ/ር ፍራንሲዮስ ንዳይሺሚዬ በኔፕ ፕላስ ቢሮ በመገኘት ከስራ
አስኪያጁ እና የስራ ክፍል ሃላፊዎች ጋር ተወያዩ፡፡ ካንትሪ ዳይሬክተሯ ማክሰኞ ግንቦት 2/2015 በኔፕፕላስ ቢሮ ባደረጉት
ጉብኝት የኔፕ ፕላስን ስትራቴጂክ ፕላን በመከለስ ዙሪያ፤ የኔፕፕላስን 20ኛ አመት አከባበር በተመለከተ እንዲሁም
ለኔፕፕላስ ሰራተኞችን መቅጠር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ሰፊ ውይይት አድርገዋል፡፡
የውይይት መድረኩን የከፈቱት የኔፕፕላስ ዋና ዳይሬክተር አቶ ካሳሁን ታደሰ ሲሆኑ፤ ዩኤን ኤድስ የኢትዮጵያ ተጠሪ እና
በአለም አቀፍ ደረጃ የምንሰማበት ድምጽ በመሆኑ በጣም የምንኮራበት አጋራችን ነው ብለዋል፡፡ በአለም አቀፍ ደረጃ
የተቀመጠውን በኤች አይ ቪ ምክንያት የሚከሰት ሞትን፤ አድሎና መገለልን እንዲሁም አዲስ የኤች አይቪ የመያዝ ቁጥርን
ዜሮ የማድረስ እቅድን ለማሳካት በጋራ በመስራታችን እድለኞች ነን ብለዋል አቶ ካሳሁን፡፡ አያይዘውም ኔፕ ፕላስ
የተቋቋመለትን አላማ ከግብ ለማድረስ በተለያየ መልኩ ራሱን እያሻሻለ እንደሚገኝ የገለጹ ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥም
የድርጅቱን እስትራቴጅክ ዕቅድ ለመከለስ መዘጋጀቱ ተጠቃሽ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡፡ ኔፕ ፕላስ ብሄራዊ ስትራቴጂክ ዕቅዱ
በሚከለስበት ወቅትም ኔፕ ፕላስ ተሳትፎ ማድረጉንም አቶ ካሳሁን ጨምረው ገልዋል፡፡
ዶ/ር ፍራንሲዮስ እና አቶ እሸት ደገፋ ከአቶ ካሳሁን ታደሰ ጋር ውይይት ሲያደርጉ
ዶ/ር ፍራንሲዮስ፤ ዩ ኤን ኤድስ እንደ ድርጅት ኔፕ ፕላስን እንደ ቤቱ ነው የሚቆጥረው ያሉ ሲሆን፤ የቫይረሱን ስርጭት
ለመግታት በሚደረገው ርብርብ ላይ በጋራ ለመስራት ሙሉ ዝግጁነታቸውን አብራርተዋል፡፡ ድርጅታቸው ምንም እንኳን
በገንዘብ ድጋፍ ማያደርግ ድርጅት ቢሆንም፤ ኔፕ ፕላስ ገንዘብ ሊያገኝ በሚችልበት ሁኔታ ላይ እና በቴክኒክ ለማገዝ
ፈቃደኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡ ከኔፕ ፕላስ የሚጠበቀውም ጥሩ ፕሮፖዛሎችን ማዘጋጀት እና የሚገኘውን ገንዘብም
በአግባቡ ፤ ግልጽነትና ተጠያቂነት በሰፈነበት እንዲሁም ሃላፊነት በተሞላበት መንገድ መጠቀም እንደሆነም አስረግጠው
ተናግረዋል፡፡ ቫይረሱ በደማቸው ያለ ወገኖች የተሻለ እና የተስተካከለ ህይወት መምራት እና የሚያስፈልጓቸውን
አገልግሎቶችም ያለ ምንም ችግር ማግኘት ይገባቸዋል ያሉት ዶ/ር ፍራንሲዮስ፤ በአሁኑ ወቅት ህክምናው በነጻ በመሰጠት
ላይ በመሆኑ አንድም ሰው በኤች አይ ቪ ምክንያት መሞት እንደሌለበትም ተናግረዋል፡፡ ኔፕፕላስም ሆነ ዩ ኤን ኤድስ ዋና
ተግባራቸው ሊሆን የሚገባው ከኤች አ ይ ቪ ጋር ተያይዞ የሚፈጠር አድሎና መገለልን ማስወገድ እንደሆነም ዳይሬክተሯ
ጠቁመዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ግጭቶች ባሉባቸው አካባቢዎች ሰብኣዊ ቀውስ አለ ሲባል በሁሉም አእምሮ ውስጥ የሚመጣው ስለሌሎች
በሽታዎች እንጂ ስለ ኤች አይ ቪ እንዳልሆነ ፤ ነገር ግን ቫይረሱ ያለባቸው ወገኖች ከየትኛውም ህብረተሰብ ክፍል የበለጠ
እየተጎዱ እንደሆነም ዳይሬክተሯ ጨምረው ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ማህበራትም ሆኑ ኔትዎርኮች ከኤች አይ ቪ የጸዳ
ትውልድ እንዲፈጠር እና አድሎና መገለልም እንዲቀንስ ስለጉዳዩ ደጋግመው መነጋገር እና በርትተው መስራት
እንደሚገባቸው ገልጸዋል፡፡ በሃገሪቱ በሚገኙ የተወሰኑ አካባቢዎች ያሉ ማህበራትን የመጎብኘት እድሉ እንደነበራቸው
የገለጹት ካንትሪ ዳይሬክተሯ፤ ኤች አይ ቪን በከመቆጣጠር እና ስርጭቱን በመከላከል ስራ ውስጥ የማህበራት መኖር
ወሳኝ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ በተጨማሪም ከማህበረሰቡ ጋር መስራት ካልተቻለ ኤች አይ ቪን የመከላከል ስራው
ውጤታማ እንደማይሆንም አስረድተዋል፡፡
ለኤች አይ ቪ እና ተያያዥ ጉዳዮች ብዙም ትኩረት ባለመሰጠቱ ጉዳይ ላይ የተስማሙት አቶ ካሳሁን፤ ደርጅቱን ስትራቴጂክ
ዕቅድ መከለስ ያስፈለገውም ከዚህ ጋር በተያያዘ መልኩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የኤ ች አይ ቪን ጉዳይ እንደ አዲስ ማንቀሳቀስ
እና ግንዛቤ ማስጨበጥ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንደሚያስፈልግም ተጠቅሷል፡፡ ይሄንን ለማድረግም የድርጅቱ
20ኛ አመት አከባበር ወሳኝ መሆኑም ተገልጿል፡፡ ክብረ በአሉ የድርጅቱን እንቅስቃሴዎች ለመላው አለም ለማስተዋወቅ
እና ቫይረሱ ያለባቸውን ወገኖች ድምጽ ለማሰማት መልካም አጋጣሚ እንደሚሆንም አስረድተዋል፡፡ በዩኤን ኤድስ
የEquality for all officer አቶ እሸት ደገፋ በበኩላቸው፤ ኔፕፕላስ በሚሰራቸው ስራዎች በርካቶችን መድረስ የቻለ እና
የብዙዎችን ህይወት መለወጥ የቻለ ተቋም በመሆኑ በቀጣይም አብሮ ለመስራት ሙሉ ዝግጁነታቸውን ገልጸዋል፡፡ እንደ
ባለሞያም ኔፕ ፕላስ እገዛ በሚያስፈልገው ጊዜ ሁሉ ለማገዝ ፈቃደኛ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡
የኔፕ ፕላስ ህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ሃላፊ አቶ ጌታቸው ጎንፋ በበኩላቸው ዩ ኤን ኤድስ እና ኔፕ ፕላስ የኤች አይ ቪን
ስርጭት ለመቀነስ በሚሰሩ ስራዎች ረገድ ለረጅም ጊዜ በጋራ በርካታ ስራዎችን ሲሰሩ እንደነበረ በማስታወስ፤ በቀጣይም
የተሻሉ በርካታ ስራዎችን ለመስራት እቅድ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ ዩ ኤን ኤድስ በቴክኒክም ሆነ በተለያዩ መንገዶች ኔፕ
ፕላስን መደገፉ የቫይረሱን ስርጭት በመግታት እንቅስቀሴው ላይ ጉልህ ሚናን እንደተጫወተም አቶ ጌታቸው ጨምረው
ገልጸዋል፡፡
ዶ/ር ፍራንሲዮስ እና አቶ እሸት ደገፋ ከኔፕፕላስ ማናጅመንት አባላት ጋር ውይይት ሲያደርጉ
የኔፕ ፕላስ ክትትልና ምዘና ክፍል ሃላፊ አቶ በላይ ረታ ደግሞ ዩ ኤን ኤድስ በኔፕ ፕላስ እንቅስቃሴ ውስጥ ከፍተኛውን
ሚና እንደተጫወተ በመጠቆም፤ ምስጋናቸውንም አቅርበዋል፡፡ ለአብነት ያህልም ኔፕ ፕላስ የግሎባል ፈንድን ግራንት
እንዲያሸንፍ ዩ ኤን ኤድስ ከፍተኛውን እገዛ እንዳደረገ በማስታወስ በቀጣይም የበለጠ አብሮ ለመስራት ዩ ኤን ኤድስ
ዝግጁ በመሆኑ ገልጸዋል፡፡
እንግዶቹ ከኔፕፕላስ ዳይሬክተር እና ከፊል ሰራተኞች ጋር
ስትራቴጂክ ዕቅድ መከለስን በተመለከተ ዩ ኤን ኤድስ የ2024/25 እቅድን በመስራት ላይ በመሆኑ በዚሁ አግባብ
እንደሚታይ ዶ/ር ፍራንሲዮስ በውይይት መድረኩ ላይ አብራርተዋል፡፡ የኤች አ ይ ቪን ጉዳይ እንደ አዲስ ማነቃቂያ
መፍጠርም ሆነ ተሰሚነትን ማምጣት እና ግንዘቤ መፍጠር ገንዘብ የሚጠይቁ ባለመሆናቸው አጠናክሮ መስራት
እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል፡፡ ኔፕ ፕላስ ከሌሎች ድርጅቶች የተለየ መሆኑን እና የቫረሱን ስርጭት በመግታቱ ረገድ
ያለውን የጎላ ሚና ማሳየት እንዳለበት አስረድተዋል፡፡ ይሄንንም የ20ኛ አመት ክብረ በአሉን በሚያከብርበት ወቅት
ተጨባች ስራዎችን በማቅረብ ምን ያህል ለውጥ ፈጣሪ መኑን ማሳየት አለበት ሲሉ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ዶ/ር ፍራንሲዮስ ዩ ኤን ኤድስ በአጠቃላይ ኔፕ ፕላስ ኤች አይ ቪን ለመከላከል በሚያደርጋቸው እንቅስቃዎች ሁሉ ከጎኑ
መሆኑን የገለጹ ሲሆን ፤ ለድርጅቱ ሰራተኛ መቅጠር ከፍተኛ ወጪ እና ሃላፊነት የሚጠይቅ በመሆኑ አሁን ላይ ይሄን
ለማድረግ ቃል መግባት እንደማይቸሉ ገልጸው፤ ነገር ግን ሃብት በማፈላለግ ስራው ላይ በሙሉ ፈቃደኝነት
እንደሚሳተፉ አስረድተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በሃገሪቱ በተለይ በትግራይ ክልል ከፍተኛ የኮንዶም እጥረት መኖሩን በመጥቀስ
ዩ ኤን ኤድስ ምን አስቧል ተብለው የተጠየቁት ዶ/ር ፍራንሲዮስ፤ አሁን ላይ ኮንዶምን በተመለከተ ያለው ችግር የገንዘብ
ሳይሆን የጥራት ጉዳይ ነው ያሉ ሲሆን፤ ጉዳዩ በሌላ አካል የሚታይ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ካንትሪ ዳይሬክተሯ በቀጣይም
ከኔፕ ፕላስ ጋር መሰል ውይይቶችን በየ ሁለት ወሩ ለማድረግም ስምምነታቸውን ገልጸዋል፡፡