ትኩረት ቫይረሱ በደማቸው ለሚገኝባቸው ማህበራት!!!!

ኤች.አይቪ/ኤድስ በዓለማችን ብሎም በሀገራችን ላይ ላፉት ሰላሳና አርባ ዓመታት ያህል  በግልና ቤተሰብ እንደዚሁ በማህበረሰብና በሀገር ላይ በጤና ፣ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳይ ላይ አስከፊ ጉዳት ሲያደርስ ቆይቷል፡፡

መንግስታት ለዚህ ዘርና ቀልም ለማይለየው ወረርሽኝ ምላሽ ለመስጠት  ባደረጉት       ርብርብ  እጅግ    በጣም   ጥሩ የሚባል ውጤት አምጥተው ወረርሽኙን ጥሩ በሚባል ደረጃ  ለመቆጣጠር ተችሎ ነበር፡፡ በዚህ ውጤታማ እንቅስቃሴ ውስጥም ቫይረሱ በደማቸው የሚገኝባቸው ወገኖች ሰፊ ድርሻ ማበርከታቸው በሁሉም ዘንድ የተመሰከረለት ጉዳይ ነው፡፡

በተለይ በሀገራች የወረርሽኙን መከሰት ተከትሎ እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች በግለሰብ ደረጃ ወደ አደባባይ በመውጣት ትውልድ ይዳን በእኔ ይብቃ በሚል መርህ የምስክርነታቸውን  ቃል  ሠጥተው  ዜጎች ራሳቸውን ከወረርሽኙ እንዲጠብቁ  አድርገዋል፡፡

እነዚህ ኤድስ ላይ የዘመቱ ጀግኖች የችግሩን ስፋት በመገንዘብ ከተበታተነ ይልቅ ባንድ ያበረ ድምጽ  ለውጥ  እንደሚያመጣ  ተረድተው ራሳቸውን በማህበር በማዋቀር ወረርሽኙን ሲዋጉ ቆይተው ማህበራት ክልላዊ ጥምረቶችንና ብሄራዊ  ጥምረትን  ፈጥረው  ማህበረሰቡን ከኤድስ ሲታደጉና ለራሳቸውም መብት ሲታገሉም ቆይተዋል፡፡ ለዚህ ስራ መሳካትም ድጋፍ ሲያደርጉልን የቆዩትን የመንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትን ቫይረሱ በደማቸው በሚገኝባቸውና ባንድ ወቅት ማህበረሰቡን ሲያስተምሩ ለነበሩና አሁን በህይወት በሌሉ ጀግኖች የማህበር አባሎቻችን ስም ሳላመሰግን አላልፍም፡፡

ማህበራትና ጥምረቶች ወረርሽኙን  ከመንግስት ጎን ቆመው ከመከላከልና ከመቆ ጣጠር ባሻገር በቫይረሱ ምክንያት እቤት የዋሉ አቅመ ደካሞችንና በዚሁ በሽታ ወላጆቻቸውን ያጡ ችግረኛ ህጻናት የጤናና የኢኮኖሚ ድጋፍ  የሚያገኙበትን የግልና ተቋማዊ የገቢ ማስገኛ ዘዴዎችን በመፍጠር የእለት ጉርስ እንዲያገኙና ልጆች ትምህርት ቤት መሄድ እንዲችሉ አድርገዋል፡፡

ሆኖም እነዚህ ማህበራት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ በመጣው የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፍ ምክንያት በርካታ አባሎቻቸው ከእይታ እየጠፉና የማህበራቱም ንቁ ተሳትፎ እየደበዘዘ መጥቷል፡፡

አሁን እንደ አዲስ እያገረሸ የመጣውን የኤች.አይ.ቪ ስርጭት እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ በጋራ በተቀናጀ መንገድ ለመመከት የእነዚህ ማህበራት መጠናከር ወሳኝ ነው ብለን እናምናለን፡፡ ስለሆነም አሁን ላይ በተበጣጠሰ መልኩ በተለያዩ ክልሎች እየተመደበ ያለው የሁለት በመቶ የኤድስ በጀት ወጥነትና ዘለቄታን በተላበሰ መልኩ ተግባራዊ በማድረግ ማህበራት ተጠናክረው ወረርሽኙን በመግታትም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ጥንካሬን የሚሰጧቸው የተለያዩ ድጋፎች እንዲያገኙ በማድረግ ዳግም ማህበራቱ ወደ ንቁ እንቅስቃሴያቸው የሚመጡበት መንገድ እንዲመቻች የፌደራልንም ሆነ የክልል መንግስታትን በአንክሮ እንጠይቃለን፡፡

መልካም ንባብ